ኢትዮጵያ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ለመሙላት የሌላ ወገን ፈቃድን እንድትጠይቅ የሚያስገድድ ዓለም አቀፍ ህግ አለመኖሩን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ ምሁራን ተናገሩ

0
62

ግድቡን በሚመለከት ቀጣይ የድርድር ጥያቄ መቅረብ ያለበት ከታችኛው ተፋሰስ አገራት እንጂ ከኢትዮጵያ መሆን እንደሌለበትም ጨምረው ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ ሲያደርጉት በቆዩት የሶስትዮሸ ድርድር ዙሪያ የታዩ ተግዳሮቶችና የቀጣይ አቅጣጫዎችን የሚመለከት የፓናል ውይይት ዛሬ አካሄዷል።

ውይይቱ የተዘጋጀው በዩኒቨርሲቲው የህግና አስተዳደር ኮሌጅ አማካኝነት ነው ።

የኮሌጁ ሶስት የህግና ጂኦ-ፖለቲካ ምሁራን ለውይይት መነሻ የሚሆን ጽሁፍ አቅርበዋል።

የጂኦ ፖለቲካ ምሁሩ ፕሮፌሰር ተስፋዬ ታፈሰ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ በዓለም ላይ ከሚገኙ በርካታ ተፋሰሶች መካከል የናይል ወንዝ ዘመናትን የተሻገረ ኢ-ፍትሃዊ አጠቃቀምን አስተናግዷል።

“ኢትዮጵያ ይህን ሁነት ለመለወጥ በርካታ ጥረቶችን አድርጋለች፤ እያደረገችም ትገኛለች” ብለዋል።

የናይል ትብብር ማእቀፍም ለዚህ ዋነኛ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው፤ የታችኛው ተፋሰስ አገራት በተለይ ግብጽ ይህ እንዳይሳካ በርካታ መሰናክሎችን ፈጥራለች ነው ያሉት።

ግብጽ የላይኛው ተፋሰስ አገራት ያልተሳተፉባቸውን የቅኝ ግዛት ውሎችን እንደ ቀይ መስመር በመዘርጋት በወንዙ ላይ ያለው ኢ-ፍትሃዊ አጠቃቀም እንዲቀጥል እየሰራች መሆኑንም አብራርተዋል።

በህዳሴ ግድቡ ላይ በተደረጉ ድርድሮች ይህን የተለመደ አቋሟን ይዛ መቅረቧን በመጠቆም።

ሌላኛው ምሁር ዶክተር ደረጀ ዘለቀ በበኩላቸው በቅርቡ በዋሽንግተን ዲሲ  ሲደረግ በነበረው ድርድር አሜሪካ ከታዛቢነት ወደ ፍርድ ሰጪነት የተሸጋገረ አድሏዊ አቋም ማንጸባረቋን ተናግረዋል። በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ የወሰደችው አቋም ትክክልና ሉዓላዊ መብቷን ያስጠበቀ ነው ብለዋል።

ነገር ግን የተፈጠሩ ልዩነቶችን በሰላም ከመፍታት ውጭ ሌላ አማራጭ መኖር እንደሌለበት መክረዋል። ኢትዮጵያ በቀጣይ ወደ ደርድር መግባት ያለባት ከግርጌ አገራት ጥያቄው ሲቀርብላት ብቻ መሆን እንዳለበትም አብራርተዋል።  

ወደ ቀጣይ ድርድር ከመግባቱ በፊት ኢትዮጵያ በወንዙ ላይ የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ድርሻ እንዳላት መተማማን ላይ መድረስ እንዳለበትም ዶክተር ደረጄ ገልጸዋል።

“ሉዓላዊ አገራት ወንዞቻቸውን ጨምሮ ውስጣቸው ለሚሰሩት ልማት የሌላ ወገን ፈቃድ እንዲጠይቁ  የሚያስገድድ ዓለም አቀፋዊ ህግ የለም” ያሉት ደግሞ የህግ ምሁሩ ዶክተር ታደሰ ካሳ ናቸው።

ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብን ለሙመላትም ሆነ ወደ ስራ ለማስገባት የሌለ አገር ፈቃድ አያሻትም ብለዋል። ነገር ግን አጠቃላይ ሂደቱ በታችኛው ተፋሰስ አገራት ላይ ጉልህ የሚባል ተጽእኖ ማሳደር እንደሌለበት አውስተዋል።

ኢትዮጵያ ግድቡን በሚመለከትም ወደ ድርድር የገባችውም ካላት ቀና አስተሳሰብ መሆኑን በመግለጽ። ኢትዮጵያዊያን ያላቸውን ልዩነት ወደ ጎን በመተው በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ የጋራ አቋም መያዝ እንዳለባቸውም ጥሪ አቅርበዋል።

አዉሎ ሚድያ መጋቢት 05/2012 ዓ.ም

መልስ አስቀምጥ

Please enter your comment!
እባክዎ ስምዎን እዚህ ያስገቡ