በግድቡ ዙሪያ የአሜሪካ አቋም ሚዛናዊ እንዳልሆነ የአገሪቷ ምክር ቤቱ አባል ተናገሩ

0
107

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የአሜሪካ መንግሥት የያዘው አቋም ሚዛናዊ እንዳልሆነ የአገሪቷ ምክር ቤቱ አባል አሳሰቡ፡፡

የምክር ቤቱ አባል ስቴቨን ሆርስፎርድ በምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ በመገኘት ማብራሪያ ለሰጡት ለአሜሪካ ግምጃ ቤት ሚኒስትር ባቀረቡት ጥያቄ፤ በአሜሪካና በዓለም ባንክ ታዛቢነት በኢትዮጵያ፣ በግብጽና በሱዳን መካከል ሲደረግ የነበረው ውይይት ሚዛናዊ፣ የሁሉም ወገን ድምጽ የተሰማበትና አገራቱን ደስተኛ ሊያደርጋቸው በሚችል ስምምነት ላይ እንዲደርሱ አሜሪካ ምን እየሰራች ነው? ሲሉ ሞግተዋቸዋል።

“እኔ እንደሚገባኝ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ የአሜሪካ መንግሥት ሚዛናዊ አቋም ይዞ ነው በውይይቱ የሚሳተፈው። በውይይቱም ቅድሚያ የምንሰጠው ለሦስቱ ሀገራት ማለትም ለኢትዮጵያ፣ ለግብጽና ለሱዳን ፍላጎት ነው።” ያሉት የምክር ቤቱ አባል፤ “የአሜሪካ መንግሥት አቋም ሚዛናዊ እንዳልሆነና ኢትዮጵያ ላይ ጫና እያሳደረች ስለመሆኑ እየተሰማ ነው” በማለትም በቂ ማብራሪያ ከሚኒስትሩ እንዲሰጣቸው በተደጋጋሚ ጠይቀዋል።

በተለይም የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት በግድቡ የውሃ ሙሊትና የሀይል ማመንጨት ሥራ አጀማመር በተመለከተ የአሜሪካ ግምጃ ቤት ያቀረበውን ሀሳብ እንደማትቀበለው መግለጿን የጠቀሱት የምክር ቤቱ አባል፤ የአሜሪካ መንግሥት ሁሉም አካላት ደስተኛ እንዲሆኑና ድምጻቸው እንዲሰማ ለማድረግ ቢሰራ ኢትዮጵያ ወደ ውይይቱ ትመለሳለች ሲሉም ያላቸውን እምነት ገልፀዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘም በኢትዮጵያ የቀድሞ  የአሜሪካ አምባሳደር ዴቪድ ሺን በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ የአሜሪካ መንግሥት እያደረገ ያለውን ጣልቃ ገብነት ተቃውመዋል። የትራምፕ አስተዳደር በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የግብጽን ጥቅም ለማስጠበቅ እየሰራ ነው ያሉት አምባሳደር ዴቪድ ሺን፤ ይህ ተግባር ተገቢነት የጎደለው ነው ብለዋል።

አዉሎ ሚድያ የካቲት 26/2012 ዓ.ም

መልስ አስቀምጥ

Please enter your comment!
እባክዎ ስምዎን እዚህ ያስገቡ