ከግብር ከፋዮች ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ ውዝፍ ዕዳ ይጠበቃል ተባለ

0
68

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ በከተማዋ ከ13 ሺ በላይ ግብር ከፋዮች ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ ውዝፍ ዕዳ እንዳለባቸው አስታወቀ።

በቢሮው የእቅድና በጀት ዝግጅት፣ ክትትልና ግምገማ ዳይሬክተር አቶ ጥላሁን ግርማ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ባለፉት ሰባት ወራት 4ሺ940 ግብር ከፋዮች 778 ሚሊዮን 295 ሺ 900 ብር ያለባቸውን ውዝፍ ዕዳ ሲከፍሉ በአንጻሩ 13ሺ 45 ግብር ከፋዮች ያለባቸውን አምስት ቢሊዮን 067ሚሊዮን 358 ሺ 343 ብር ውዝፍ ዕዳ አልከፈሉም።

ዳይሬክተሩ እንዳብራሩት፤ በከተማዋ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ግብር ከፋይ ውዝፍ ዕዳ ያለበት በመሆኑ፤ በተያዘው በጀት ዓመት ችግሩን በመቅረፍ የከተማ አስተዳደሩን ገቢ ለማሳደግ በአስተዳደሩ ካቢኔ ውሳኔ መሰረት ውዝፍ እዳ ያለባቸው ግብር ከፋዮች ወለድና ቅጣቱ ቀርቶ ከጥቅምት ወር 2012 ዓ.ም አስከ ሰኔ 30 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ ፍሬ ግብሩን ብቻ እንዲከፍሉ የዕዳ ማጽጃ ስርዓት መዘርጋቱን ተናግረዋል።

ይህን መልካም ዕድል ተጠቅመው ያለባቸውን ውዝፍ ዕዳ እየከፈሉ ያሉ ግብር ከፋዮቹ ቁጥራቸው አነስተኛ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ጥላሁን፤ ባለፉት ሰባት ወራት 4ሺ940 ግብር ከፋዮች 778 ሚሊዮን 295 ሺ 900 ብር ያለባቸውን ውዝፍ ዕዳ ቢከፍሉም 13,045 ግብር ከፋዮች ያለባቸውን አምስት ቢሊዮን 67ሚሊዮን 358 ሺ 343 ብር ውዝፍ ዕዳ አለመክፈላቸውን ገልጸዋል።

አቶ ጥላሁን ወለድና ቅጣቱ ሲነሳ ግብር ከፋዩ የሚከፍለው ፍሬ ግብር በጣም አነስተኛ መሆኑን ጠቁመው፤ ግብር ከፋዮች የዕዳ ማጽጃ ስርዓቱን በመጠቀም የሚጠበቅባቸውን ውዝፍ እዳ ከፍለው ከዕዳ ነጻ ሊሆኑ ይገባል። ነገርግን ግብር ከፋዩ ይሄንን መልካም ዕድል ተጠቅሞ በተቀመጠው ጊዜ ገደብ ውስጥ ወደ ስርዓቱ መመለስ ካልቻለ ቢሮው አስተዳደራዊ ቅጣት በመጣል ግብሩን ለመሰብሰብ ይገደዳል ብለዋል።

 በከተማ አስተዳደሩ አመቻችነት ከሦስት ሺ በላይ ከሚሆኑ ውዝፍ ዕዳ ካለባቸው ግብር ከፋዮች ጋር ከዚህ በፊት ውይይት መደረጉን አቶ ጥላሁን ጠቁመው፤ ግብር ከፋዮች የዕዳ ማጽጃ ስርዓቱን በመጠቀም የሚጠበቅባቸውን ውዝፍ እዳ ከፍለው ከዕዳ ነጻ እንዲሆኑ በየቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ከግብር ከፋዮች ጋር በተናጠል ውይይት እየተደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

አዉሎ ሚድያ የካቲት 25/2012 ዓ.ም

መልስ አስቀምጥ

Please enter your comment!
እባክዎ ስምዎን እዚህ ያስገቡ