በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ለማዋል እየተሰራ ነው- የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ

0
95

የተለያዩ ወንጀሎችን ሰርተው በብሄር፣ በኃይማኖት፣ በፖለቲካ ፓርቲዎችና በተለያዩ ቡድኖችና በየክልሎቹ የተደበቁ ተጠርጣሪዎችን በህግ ፊት ለማቅረብ በመንግሥት ቁርጠኛ አቋም ተይዞ እየሰራ ነው ብሏል የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ። 

በመስሪያ ቤቱ የህዝብ ግንኙነትና የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ዝናቡ ቱኑ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ የተለያዩ ወንጀሎችን ሰርተው በብሄር፣ በኃይማኖት፣ በፖለቲካ ፓርቲዎችና ቡድኖች ሽፋን በየክልሎቹ የተደበቁ ተጠርጣሪዎችንና ከዚህ ቀደም ምርመራ ተካሂዶባቸውና መያዣ ወጥቶባቸው በቁጥጥር ስር ያልዋሉ ተጠርጣሪዎችን ጭምር በህግ ፊት ለማቅረብ ንግሥት ከወትሮው በተለየ ቁርጠኛ አቋም ይዞ እየሰራ ነው።

በተለያዩ ወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በህግ ፊት ከማቅረብ አኳያ ከዚህ በፊት የተስተዋሉ ጠንካራና ደካማ ጎኖችን የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኙበት የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች በጋራ መገምገሙን የሚናገሩት ዳይሬክተሩ፤ የክልል የጸጥታ አካላት በአካባቢያቸው በተለያዩ ወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በህግ ፊት ለማቅረብ ኃላፊነቱን ወስደው ተጠርጣሪዎች እንዲያዙ የማድረግ ስራዎች ላይ በስፋት እየሰሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ዳይሬክተሩ ግጭቶች በተከሰቱባቸው አካባቢዎች በተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች ከተጠረጠሩ ከሶስት ሺ 606 ግለሰቦች ውስጥ አንድ ሺ 682 የሚሆኑትን በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ መሆኑን ገልጸው፤ በቀጣይ በቁጥጥር ስር ያልዋሉትን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በቁጥጥር ስር ውለው ለህግ እንዲቀርቡ የማድረግ ሥራ መንግሥት ከወትሮው በተለየ ቁርጠኛ አቋም ይዞ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

አቃቤ ህግ ከክልል የጸጥታ አካላትና ከፌዴራል ፖሊስ ጋር ተቀናጅቶ በመስራት ማናቸውንም ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ለማዋል እየሰራ መሆኑን አቶ ዝናቡ ጠቁመው፤ የክልል የጸጥታ አካላት ወንጀል ፈጽመው በክልሉ የመሸጉ ወንጀለኞችን በህግ ፊት ለማቅረብ በቁርጠኝነት እንዲሰሩ አቅጣጫ ተሰጥቷቸዋል። የክልል የጸጥታ አካላት በተሰጠው አቅጣጫ መሰረት ተጠርጣሪዎችን ይዘው ለህግ የማያቀርቡ ከሆነ በተሰጣቸው ኃላፊነት ልክ ተጠያቂ የሚሆኑበት አሰራርመዘርጋቱን ተናግረዋል።

በአጠቃላይ በከባድ የሙስና ወንጀል፣ በሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ በግድያ፣ ማንነትን መሰረት ባደረጉ ዘረፋዎች፣ በአስገድዶ መድፈር፣ በኃይማኖት ተቋማት ላይ ጥቃት ያደረሱ እና የብሄር ግጭት ለመፍጠር በቀጥታ ሲሰሩ የነበሩ ተጠርጣሪዎችን በሙሉ በቁጥጥር ስር በማዋል በህግ ፊት ለማቅረብ የፌዴራልና የክልል የጸጥታ አካላት በጋራ ጠንካራ አቋም ይዘው እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ በተለያዩ ወንጀሎች ተጠርጥረው በህግ ጥላ ሥር ሆነው የክስ ሂደታቸውን ሲከታተሉ የነበሩ 63 ተጠርጣሪዎችን ለአገራዊ አንድነትና ለለውጡ የሚኖረውን ፋይዳ ግምት ውስጥ በማስገባት ከሰሞኑ ክሳቸው እንዲቋረጥ ማድረጉ ይታወሳል።

አዉሎ ሚድያ የካቲት 25/2012 ዓ.ም

መልስ አስቀምጥ

Please enter your comment!
እባክዎ ስምዎን እዚህ ያስገቡ