በኢትዮጵያ 1459 የቡና ናሙና መሰብሰቡን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ

0
632

በኢትዮጵያ በቅርቡ ለሚካሄደው በባለ ልዩ ጣዕም የቡና ቅምሻ ውድድር አንድ ሺ 459 የቡና ናሙና መሰብሰቡንና ናሙናው በመጠን ከፍተኛ እንደሆነም የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ።

ባለስልጣኑ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ በቅርቡ የባለ ልዩ ጣዕም ቡና ቅምሻ ውድድር ለማካሄድ በሚደረገው ዝግጅት ላይ ከመላው ሀገሪቱ የሚመጡ የቡና ናሙናዎች የሚቀርቡ ሲሆን፣ቡና አምራቾች፣ላኪዎች፣አቀናባሪዎች፣የህብረት ሥራ ማህበራት፣ቡና ማጠቢያ ጣቢያዎች ናሙናቸውን አስገብተዋል።

ከጥር 25-29 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ አንድ ሺ 459 የቡና ናሙና ተሰብስቧል ያለው መግለጫው፤ ውድድሩ በቡና ዘርፉ ለተሰማሩ በተለይም ለአርሶ አደሮችና አልሚዎች ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረውና ለአገሪቱም የተሻለ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት እንደሚያግዝ አመልክቷል።

ባለስልጣኑ ከአሜሪካን ተራድኦ የምግብ ዋስትና ጋር በመተባበር በዓለም ታዋቂ የሆነውንና‹‹ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ››የተባለውን የባለ ልዩ ጣዕም የቡና ቅምሻ ውድድር ወደ ኢትዮጵያ በከፍተኛ ጥረት ለማምጣት መቻሉን አመልክቷል። ውድድሩ ዓለም አቀፍ

 እውቅና ባላቸው ባለሙያዎች እንደሚዳኝና ዓለም አቀፍ ቡና ገዢዎችንም ይስባል ተብሎ እንደሚጠበቅ በመግለጫው ተመልክቷል።

በውድድሩ የመጀመሪያ ዙር የሚያልፉ ናሙናዎች አዲስ አበባ ተልከው በሀገር ውስጥ ቡና ቀማሾች እንደሚቀመሱና 150 የሚሆኑ ሀገራዊ አሸናፊዎች ከተመረጡ በኋላ በድጋሚ በሀገር ውስጥ ቀማሾች ተቀምሰው 40 የላቁ ቡናዎች እንደሚመረጡም ተብራርቷል። ቀደም ሲል በተካሄደ የቡና ቅምሻ ውድድር አሸናፊ ሆነው የተሸጡ ቡናዎች በተደጋጋሚ የዓለም ቡና ክብረወሰን መስበር መቻላቸውን በመግለጫው ተጠቅሷል።ውድድሩ አምራቾች በጥራት እንዲያመርቱና ከዘርፉም ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንደሚያግዛቸውም ተገልጿል።

የባለስልጣኑ መግለጫ እንዳመለከተው ለውድድር የገቡት ቡናዎች የቅድመ መረጣ ስራ ከየካቲት 16-20/2012 ዓ/ም ድረስ እንዲሁም ቡናዎችን ወደ መጋዘን የማስገባት ስራው ከየካቲት 23 – መጋቢት 14/2012 ዓ/ም ድረስ ይከናወናል። ሀገራዊ የውድድር መድረኩ ደግሞ ከመጋቢት 21-25/2012 ዓ/ም ድረስ የሚካሄድ ሲሆን፤ ዓለም አቀፍ የውድድር መድረኩም ከመጋቢት 29- ሚያዝያ 2/2012 ዓ/ም እንደሚሆንና ዓለም አቀፍ ጨረታው ደግሞ ግንቦት 2012 ዓ.ም ይካሄዳል።

አዉሎ ሚድያ የካቲት 19/2012 ዓ.ም

መልስ አስቀምጥ

Please enter your comment!
እባክዎ ስምዎን እዚህ ያስገቡ