ኮሎኔል ቢኒያም ተወልደ ፤ አቶ ኤርሚያስ አመልጋ እና አቶ ክርስቲያን ታደለን ጨምሮ የ63 ተጠርጣሪዎች ክስ ተቋረጠ

0
157

የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ  በተያዩ ወንጀሎች ተጠርጥረው ታስረው የነበሩ 63 ተጠርጣሪዎች ክስ መቋረጡን አስመልክቶ   ዛሬ የካቲት 17 ቀን 2012 ዓ.ም  መግለጫ ሰጥቷል፡፡

መግለጫውን የሰጡት በተቋሙ የተደራጁና ድንበር ተሸጋሪ ወንጀሎች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ ጸጋ እንደገለጹት በተለያዩ ደረጃ የሚገኙ 63 ተጠርጣሪዎች  ክሳቸው እንዲቋረጥ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች ተጠርጥረውና ምርመራ ተጣርቶባቸው፣ ማስረጃ የተሰበሰበባቸው እና ክስ ተመስርቶባቸው በሙስና ወንጀል ከሜቴክ ጋር በተያያዘ፣ ከሰብዓዊ መብት ጥሰት ጋር የተጠርጠሩ ነገር ግን የመሪነት ሚና የሌላቸው፣ ከሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም የከፍተኛ አመራሮች ግድያ ጋር ተጠርጥረው ጉዳያቸው እየታየ ያሉ፣ ከሲዳማ፣ ቤንሻንጉል እና የሶማሌ ክልል ግጭቶች ጋር በተያያዘም የተጠረጠሩም ጭምር ክከሳቸው ከተቋረጠው መካከል እንደሚገኙ በመግለጫው ተናግረዋል፡፡

ዳይሬክተሩ እንዳሉት አጠቃላይ ከሚፈለጉት 3606 ተጠርጣሪዎች መካከል 1682 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የገለጹ ሲሆን ሌሎች በወንጀሉ ላይ በቀጥታ ተሳትፎ ያላቸው ተጠርጣሪዎችን የመያዝ ሥራ ተጠናክሮ እየተሰራ እንደሆነም አብራርተዋል፡፡

በተጨማሪም ከዚህ በኋላ በማህበራዊ ሚዲያዎች ሆነ በማንኛውም አግባብ የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃን በማሰራጨት ብሔርን፣ ሃይማኖትን፣ ማንነትን መሰረት በማድረግ ግጭትና ብጥብጥ ለመፈጠር የሚንቀሳቀሱ አካላት ለሀገር ደህንነት ሲባል በህግ ተጠያቂ እንደሚሆኑም ጠቁመዋል፡፡

አዉሎ ሚድያ የካቲት 17/2012 ዓ.ም

መልስ አስቀምጥ

Please enter your comment!
እባክዎ ስምዎን እዚህ ያስገቡ