በጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል አደም መሀመድ የተመራ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ልዑክ በሳዑዲ ዓረቢያ የስራ ጉብኝት አደረገ

0
155

በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል አደም መሀመድ የተመራና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ሚኒስትር ደዔታ ተስፋሁን ጎበዛይ እንዲሁም የአገር መከላከያ ከፍተኛ አመራሮች ያካተተ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን በሳዑዲ ዓረቢያ ሪያድ የስራ ጉብኝት አድርጓል፡፡

በቆይታውም የልዑካን ቡድኑ ከሳዑዲ አረቢያ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ፈያድ ቢን ሃመድ አል-ሩዋሊና የሳዑዲ ዓረቢያ የመከላከያ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር በመገናኘት በሁለትዮሽና ቀጠናዊ የሰላምና ጸጥታ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይቶችን አካሂዷል፡፡

በውይይቶቹ በኢትዮጵያና ሳዑዲ ዓረቢያ መካከል በመከላከያ ዘርፍ ያለውን የሁለትዮሽ ትብብር ለማጠናከርና በሌሎች ቀጠናዊ የጋራ ስጋቶች ዙሪያ በትብብር መስራትና የልምድ ልውውጥ ማድረግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ምክክርና የሃሳብ ልውውጦች ተደርገዋል፡፡

የልዑካን ቡድኑ በሪያድ የሚገኘውን የእስላማዊ ጸረ-ሽብርተኝነት ወታደራዊ ጥምረት ማዕከል (The Islamic Military Counter Terrorism Coalition (IMCTC)) ዋና ጽ/ቤት በመጎብኘትም ከማዕከሉ አመራሮች ጋር ሽብርተኝነት በመከላከል ረገድ በጋራ መስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር አድርጓል፡፡

የሳዑዲ ዓረቢያ መንግስት ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅትና የአፍሪካ ሕብረት የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ተሳትፎ ለቀጠናው ሰላምና መረጋጋት እያበረከተች ያለውን አስተዋጽኦ እንደሚያደንቅ የገለጸ ሲሆን፣ በዚህ ረገድ ለአገራችን የበኩሉን ድጋፍ ለማድረግ ያለውን ዝግጁነት አረጋግጧል፡፡

የልዑካን ቡድኑ በሪያድ የኢፌዲሪ ኤምባሲ ለኢትዮጵያውያን የሚሰጠውን የቆንስላ አገልግሎት ጎብኝቷል፡፡

ምንጭ፡የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዉሎ ሚድያ የካቲት 13/2012 ዓ.ም

መልስ አስቀምጥ

Please enter your comment!
እባክዎ ስምዎን እዚህ ያስገቡ