ቤተ-ክርስቲያን ህገ-ወጥ የአምልኮ ቦታ ነው በሚል በተወሰደ እርምጃ ህይወታቸውን ላጡ ምዕመናን ተጠያቂ የሆኑ አካላት ለፍርድ እንዲቀርቡ ጠየቀች

0
86

በቅርቡ በአዲስ አበባ ህገ-ወጥ ነው በሚል ቤተ-ክርስቲያን ለማፍረስ በተወሰደው እርምጃ ህይወታቸው ላለፉ ምዕመናን ተጠያቂ የሆኑ አካላት ለፍርድ እንዲቀርቡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ጠየቀች፡፡

ቤተ-ክርስቲያኗ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከሰሞኑ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ለሚኖሩ ምዕመናን የቤተ-ክርስቲያን መስሪያ ቦታ በማስፈቀዳቸው አመስግናለች።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ሲያካሄድ የነበረውን አስቸኳይ ጉባኤ ዛሬ አጠናቅቆ የአቋም መግለጫ አውጥቷል።

በመግለጫው ጥር 24 ቀን 2012 ዓ.ም ሌሊት በቦሌ ቅዱስ ገብርኤልና ቅድስት አርሴማ ቤተ-ክርስቲያን ህገ ወጥ ይዞታ ነው በሚል የጸጥታ አካላት በወሰዱት እርምጃ የዜጎች ህይወት ማለፉን አስታውሶ ድርጊቱን የፈፀሙት ለህግ እንዲቀርቡና የምርምራ ውጤቱም ለምዕመኑ ይፋ እንዲደረግ ሲኖዶሱ ጠይቋል።

ከዚህ በተጨማሪ ቤተ-ክርስቲያኗ ቦታ ተሰጥቷት ቤተ-ክርስቲያን መገንባት እንድትችልም ሲኖዶሱ ጠይቋል።

ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የታሰሩ ካህናትና ምዕመናን ከእስር እንዲፈቱም ነው ቅዱስ ሲኖዶሱ የጠየቀው።

በተጨማሪ በአንዳንድ የቤተ-ክርስቲያኗ ገዳማት ላይ ችግር የሚፈጥሩ ግለሰቦች በመንግስት እርምጃ እንዲወሰድባቸው ሲኖዶሱ መጠየቁን ቅዱስ ፓትሪያርኩ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ በመግለጫው ገልጸዋል።

አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ላይ አሉታዊ ተጽእኖ የሚያደርሱ ዘገባዎችን እያቀረቡ መሆኑንና ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም አሳስበዋል።

አዉሎ ሚድያ የካቲት 12/2012 ዓ.ም

መልስ አስቀምጥ

Please enter your comment!
እባክዎ ስምዎን እዚህ ያስገቡ