በአዲስ አበባ ፈጣን የኢንተርኔት አገልግሎት ተጀመረ

0
122

ኢትዮ-ቴሌኮም የታሪፍ ማሻሻያ ከተደረገ በኋላ የኢንተርኔት ትራፊክ በ196፣ የድምጽ ትራፊክ በ62 በመቶ ማደጉን አስታወቀ።

የኢትዮ-ቴሊኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወይዘሪት ፍሬህይወት ታምሩ፤ ድርጅቱ በአዲስ አበባ ሙሉ በሙሉ የፎር ጂ አገልግሎት ማስፋፊያ እና የኤል.ቲ.ኢ አድቫንስ የተባለ ፈጣን የኢንተርኔት አገልግሎት የሚሰጥ ፕሮጀክት ትናንት ባስመረቀበት ወቅት እንደተናገሩት፤ የታሪፍ ማሻሻያው ተግባራዊ ሲደረግ የኢንተርኔት ትራፊክ በ169 በመቶ የድምጽ ትራፊክ ደግሞ 62 ነጥብ 6 በመቶ አድገዋል።

የደንበኞች የአገልግሎት ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን ጠቅሰው፣ባለፉት ስድስት ወራት የኢንተርኔት ትራፊክ 82 በመቶ የድምጽ 22 በመቶ ማደጉን አስታውቀዋል።ድርጅቱ የደንበኞቹን ፍላጎት በጥራትና በተመጣጣኝ ዋጋ ለማሟላት ማስፋፊያ እያደረገ መሆኑን ተናግረው፣አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችንም ተግባራዊ እያደረገ መሆኑንም አመልክተዋል።

እንደ ወይዘሪት ፍሬህይወት ገለጻ፤ኢትዮ ቴሌኮም ኤል.ቲ.ኢ አድቫንስ የተባለ የኢንተርኔት አገልግሎት የሚሰጥ ቴክኖሎጂ በአዲስ አበባ በ50 ቦታዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ አድርጓል። ተግባራዊ ካደረገባቸው ቦታዎች መካከል ስድስት ኪሎ፣ ዩኒቲ ፓርክ፣ ካዛንችስ፣ ቦሌ፣ አፍሪካ ኅብረት ይጠቀሳሉ።የ4ጂ አገልግሎቱንም በአዲስ አበባ በሁሉም ቦታዎች ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ተደርጓል።

እንደ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ዘገባ ይህ የኢንተርኔት አገልግሎት ቀደም ሲል ከነበሩት የ3 ጂ የኢንተርኔት አገልግሎት በጣም ፈጣን መሆኑን አመልክተው፤ፈጣን የኢንተርኔት አገልግሎት በአዲስ አበባ የመጀመሩ ዋነኛ ምክንያት የደንበኞች ፍላጎት መጨመር መሆኑን ገልጸዋል።በቀጣይም የደንበኞች ፍላጎትን መሰረት አድርጎ ማንኛውንም ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተግባራዊ ለማድረግ ድርጅታቸው ዝግጁ መሆኑም አመልክተዋል።

እንደ ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ማብራሪያ፤ በአዲስ አበባ ተግባራዊ የተደረገው ፕሮጀክት በከተማዋ እያደገ የመጣውን የኢንተርኔት የደንበኞች ፍላጎት ማርካት ያስችላል። ለፕሮጀክቱ 173 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎበታል።ወጪው የተሸፈነውም በኢትዮ ቴሊኮም ነው። ፕሮጀክቱ በ10 ቀናት ውስጥ የተጠናቀቀ ሲሆን፣ ቴክኖሎጂው የኢንተርኔት አገልግሎት አጠቃቀምን ፈጣን ያደርጋል።

የክልል ከተሞችንም የፈጣን የኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ የ4ጂና የኢንተርኔት አገልግሎትን ለማስፋፋት እየተሰራ ነው። የአንዳንድ ከተሞች ጥናት መጠናቀቁና የሌሎች ከተሞች ጥናት እየተደረገ ነው። ኢትዮ- ቴሌኮም ከዲጅታል ኢኮኖሚ ግንባታ ጎን ለጎን ጥራትና ተመጣጣኝ ዋጋ ሞባይሎችንና አገራዊ ምርቶችን በማበልጸግ ተግባራዊ ማድረግ አለባቸውም ብለዋል።

የአዲስ አበባ ፕሮጀክትን የዘረጋው የሁዋዌ የሰሜን አፍሪካ ቀጣና ሥራ አስኪያጅ፤ ሚስተር ዲቪድ ያንግ፤ ድርጅታቸው ከኢትዮጵያ ጋር ጠንክራ ግንኙነት እንዳለው ገልጸው፣በቀጣይም ይህንኑ ተግባሩን ሁለቱንም ተቋማት ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ እንደሚቀጥልም አመልክተዋል።

አዉሎ ሚድያ ጥር 26/2012 ዓ.ም

መልስ አስቀምጥ

Please enter your comment!
እባክዎ ስምዎን እዚህ ያስገቡ