ሶማሊያ የአንበጣ መንጋ መስፋፋትን ተከትሎ አስቸኳይ ጊዜ አዋጀች

0
157

ኢትዮጵያን ጨምሮ በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ጉዳት እያደረሰ የመጣውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል ሶማሊያ ብሄራዊ የአስቸኳይ ጊዜ አውጃለች ፡፡

የሀገሪቷ ግብርና ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ከፍተኛ መጠን ያለው እፅዋትን የሚያወድም የአንበጣ መንጋ “ለሶማሊያ የምግብ ዋስትና ዋነኛው ስጋት” ነው፡፡

የሶማሊያ መንግስት የአዝመራ ወቅት በሚያዝያ ወር ከመጀመሩ በፊት ሁኔታውን ለመቆጣጠር ሊያስቸግር እንደሚችልም ነው የጠቆመው ፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደገለጸው በ25 ዓመታት ውስጥ በሶማሊያ እና ኢትዮጵያ የተከሰተው የአንበጣ መንጋ ከፍተኛው ነው፡፡

ጎረቤት ኬንያም ብትሆን በ 70 ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ የአንበጣ መንጋ ስጋት ላይ እንደወደቀች የተባበሩት መንግስታት የምግብና እርሻ ድርጅት ገልጿል፡፡

በሶማሊያ ያልተረጋጋ የፀጥታ ሁኔታ ምክንያት አውሮፕላኖችን ተጠቅሞ የተባይ ማጥፊያዎችን ከአየር ለመርጨት ያስቸግራል የተባለ ሲሆን ሀገሪቱም የአንበጣ መንጋ ለመከላከል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያወጀች የመጀመሪያዋ ሀገር ሆናለች፡፡

የተባበሩት መንግስታት የምግብና እርሻ ድርጅት ባወጣው ሪፖርት በአፍሪካ ቀንድ የተከሰተውን እጅግ አደገኛ የአንበጣ መንጋ ለመዋጋት ዓለም አቀፍ የዕርዳታ ጥሪ ያቀረበ ሲሆን በፍጥነት መከላከል ካልተቻለ በምስራቅ አፍሪካ የአንበጦች ቁጥር እስከ ሰኔ ወር ድረስ በ500 እጥፍ ሊያድግ እንደሚችል አስጠንቅቋል፡፡

የአንበጣ መንጋው በ 2019 መገባደጃ ላይ በጣለው ከባድ ዝናብ ከየመን ቀይ ባህር ወደ ምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ተሻግሮ እንደተስፋፋ ይህም ለነፍሳቱ እድገት ምቹ የመራቢያ ሁኔታዎችን እንደፈጠረ ተጠቁሟል፡፡

አንበጣ በአንድ ቀን ውስጥ እስከ 150 ኪ.ሜ (93 ማይል) መጓዝ ይችላል፡፡

እያንዳንዱ ጎልማሳ ነፍሳት በየቀኑ የራሱን ክብደት ያህል ሊበላ እንደሚችል መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

በተለይ በኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ሶማሊያ ሀገራት ውስጥ የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል 70 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ኦክስፋም ባወጣው ሪፖርቱ መግልጹ ይታወሳል ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው ፡፡

አዉሎ ሚድያ ጥር 25/2012 ዓ.ም

መልስ አስቀምጥ

Please enter your comment!
እባክዎ ስምዎን እዚህ ያስገቡ