በኢትዮጵያ የአፍሪካ የዘረ-መል ምርመራ ማዕከል ሊገነባ ነው

0
113

የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ የአፍሪካ የዘረ-መል ምርመራ ማዕከል ለመገንባት ዝግጅት መጀመሩን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር አስታውቋል፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ጀማል በከር ከአሜሪካው ዓለም አቀፍ የልማት ፋይናንስ ኮርፖሬሽን (U.S. International Development Finance Corporation (DFC) የልኡካን ቡድን አባላት ጋር መክረዋል ፡፡

የአሜሪካው ዓለም አቀፍ የልማት ፋይናንስ ኮርፖሬሽን (DFC) ለግል ዘርፍ ልማት ኘሮጀክቶች ፋይናንስ የሚሰጥ የአሜሪካ መንግስት ኤጀንሲ ሲሆን በኢትዮጵያ የሚገነባውን የዘረ-መል ምርመራ ማዕከል የጄኔቲክ ልዩነት ተግባር ትንታኔ ላይ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በሚሰራውና በዘርፉ ዓለም አቀፍ መሪ በሆነው የአሜሪካው ጂኖሚክስ የግል ምርመራ ተቋም ኢሉሚና (Illumina) አማካኝነት ነው፡፡

የዘረ-መል ምርመራ ዲ ኤን ኤ ትልቅ ሞልዩኪል ሆኖ ህይወት ያላቸውን ማናቸውንም ፍጡራን፣አትክልት፣ እንስሳት፣ባክቴሪያ ወዘተ የዘር-ቀመር ያዘለ ነው።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ጀማል በከር ኢትዮጵያ የዘረ-መል ምርመራዎችን በውጭ ሀገራት በከፍተኛ ወጪ እንደምታሰራ ጠቅሰው የማዕከሉ መገንባት ወጪውን ከማስቀረት አልፎ ምርትና ምርታማነትን ለማሻሻል በሚደረገው ጥረት በባዮ ቴክኖሎጂ ዘርፍ አቅምን በመገንባት ቴክኖሎጂን ለማሸጋገር እና በግብርናው፣በጤና፣በኢንዱስትሪ እና በአካባቢ ልማት የሚያስፈልጉ ግብአቶችን አሟልቶ በእውቀትና በቴክኖሎጂ የተደገፈ ስራን ለመስራት ይረዳል ብለዋል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው አያይዘውም ኢትዮጵያ የአፍሪካ መዲና እንደመሆኗ መጠን በምርምር እና በባዮቴክኖሎጂ የታገዘ እንቅስቃሴ በማድረግ በኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የአፍሪካ ማዕከል ለመሆን የጀመረችውን እንቅስቃሴም ያግዛል ማለታቸውን ከሚኒስቴሩ አገኘሁት ብሎ ኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዘግቧል፡፡

አዉሎ ሚድያ ጥር 15/2012 ዓ.ም

መልስ አስቀምጥ

Please enter your comment!
እባክዎ ስምዎን እዚህ ያስገቡ