ምርጫ የሚደረግበት የመጨረሻ ቀን ወደፊት ይገለፃል ተባለ

0
219

ኢትዮጵያ ዉስጥ ምርጫ የሚደረግበት የመጨረሻ ጊዜ ወደፊት ይፋ እንደሚያደርግ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ አስታወቀ። ቦርዱ ነሐሴ 10ን ጊዚያዊ የምርጫ ቀን ማድረጉን በቅርቡ አስታዉቆ ነበር።

ኢትዮጵያ ዉስጥ ምርጫ የሚደረግበት የመጨረሻ ጊዜ ወደፊት ይፋ እንደሚያደርግ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ አስታወቀ። ቦርዱ ነሐሴ 10ን ጊያዊ የምርጫ ቀን ማድረጉን በቅርቡ አስታዉቆ ነበረ ቢሆንም ፤ የቦርዱ ቃል አቀባይ ወይዘሪት ሶሊያና ሽመልስ ዛሬ እንዳስታወቁት ግን የመጨረሻዉ የምርጫ ቀን ከፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችና «የሕብረሰብ ክፍል» ካሏቸዉ ወገኖች ጋር ቦርዱ ከተወያየ በኋላ ይወሰናል። 

ቦርዱ ያስቀመጠዉ ጊዚያዊ የምርጫ ቅስቀሳ ጊዜ ሳይጀመር የምረጡኝ ቅስቀሳ በሚያደርጉት ፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድ በመመርመር ላይ እንደኾነም የቦርዱ ቃል አቀባይ ሶሊያና ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ የዘንድሮዉ ምርጫና ዝግጅቱ የሚደረግበት ጊዚያዊ የጊዜ ሰሌዳ በቅርቡ ይፋ አድርጓል።።በጊዜ ሰሌዳዉ መሠረት ካለዉ ታሕሳስ 22 ጀምሮ የምርጫ ክልል ቢሮዎችን እያደራጀ ነዉ። የቦርዱ የተረጋገጠ ውጤት ማሳወቂያ ጊዜን ነሐሴ 20/2012 ለማድረግ ጊዚያዊ ቀጠሮ መያዙንም ነው  የጊዜ ሰሌዳ የሚያመለክተው።

የምርጫ ቦርዱ ጊዜያዊ የጊዜ ሰሌዳን ሕጋዊ እና ትክክለኛ በማለት ስምምነታቸውን የገለጹ የመኖራቸውን ያህል ምርጫዉ በከባዱ የክረምት ወቅት ይደረጋል መባሉ፣ በመንገድ መሰረተ ልማት እና የወንዞች ሙላት ምርጫው ያለ ችግር ስለመከናወኑ ጥርጣሬ የገባቸው እንዳሉም ታይቷል።

ምርጫ ቦርድ በበኩሉ የመጨረሻ በሚለው የምርጫ ማስፈጸሚያ የጊዜ ሰሌዳ ለማውጣት እየሰራ መሆኑን አስታውቋል። ቀደም ሲል ለመነሻነት ይፋ ያደረገው የጊዜ ሰሌዳ ላይ አስተያየት እያሰባሰበበት ስለመሆኑም ነው የቦርዱ ቃል አቀባይ ወ/ሪት ሶሊያና ሽመልስ ለዶይቸ ቬለ የተናገሩት ።

የብሔራዊ የምርጫ ቦርድ የምርጫ 2012 ቀነ ቀጠሮን ቁርጥ ባያደርግም የአዳዲስ ተወዳዳሪ ፓርቲዎችን ግን መመዝገቡን ቀጥሏል። ቦርዱ ዛሬ እንዳስታወቀው ለአራት ፓርቲዎች የእውቅና ምስክር ወረቀትና ጊዜያዊ የምዝገባ ፈቃድ ሰጥቷል።የእውቅና ምስክር ወረቀትና ጊዜያዊ የምዝገባ ፈቃድ የተሰጣቸው አራቱ ፓርቲዎች ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ፣ አንድ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ አማራ ጊዮናዊ ንቅናቄ እና እናት ፓርቲ ናቸው።

አዉሎ ሚድያ ጥር 14/2012 ዓ.ም

መልስ አስቀምጥ

Please enter your comment!
እባክዎ ስምዎን እዚህ ያስገቡ