የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን የከተማዋን የመንገድ መብራቶች ለማዘመን እየሰራ ነው

0
136

የከተማዋ የመንገድ መብራቶች ለማዘመን በስፋት እየሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን አስታወቀ።በግጭትና በመሳሰለው ሳቢያ አገልግሎት አቁመው የቆዩ የመንገድ መብራቶችንም እየጠገነ እንዲበሩ ማድረጉን ጠቁሟል።

የባለስልጣኑ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ጥኡማይ ወልደገብርኤል በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ ባለስልጣኑ መብራቶቹን በአዲስ ዘመናዊ አምፑሎች እየተካም ይገኛል ።ባለፉት ሁለት አመታትና በተያዘው በጀት አመትም በተለያዩ ችግሮች ሳቢያ አገልግሎት መስጠት አቁመው የነበሩ በርካታ የመንገድ ዳር መብራቶችን ጠግኖ ወደ ስራ አስገብቷል።

ባለስልጣኑ የሚያስተዳድራቸው ከ25 እስከ 26 ሺ የሚደርሱ የመንገድ ዳር መብራቶች እንዳሉ ዳይሬክተሩ ጠቅሰው፣አብዛኛዎቹ የመንገድ መብራቶች መንገዱ ሲገነባ የተሰሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል። ‹‹አንድ መንገድ 24 ሰአት እንዲያገለግል ተደርጎ ነው የሚሰራው።መንገዱ ተሰርቶ መብራት ከሌለው በሌሊት ትራፊክ ላያስተናግድ ይችላል።›› ብለዋል።

‹‹የመንገድ መብራት የመንገድ አካል ነው። ህብረተሰቡ በሌሊትም እንደ ልብ ተንቀሳቅሶ እንዲሰራ ያስችላል፤ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴም የራሱን ተጽእኖ ያሳርፋል፤ መንገድ የትራፊክ አደጋን የመቀነስ እንዲሁም ትራፊክ የማሳለጥ አቅሙም ከፍተኛ ነው።›› ሲሉ አብራርተው፣ የከተማዋን የሌሊት ገጽታ በሚገባ የሚያሳይ እንደሆነም ተናግረዋል።

ባለስልጣኑ እነዚህን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ሁለት መሰረታዊ ነገሮችን እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፣ በዚህም የመንገዶቹን መብራት ዘመኑ በደረሰበት ኤልኢዲ ላይት በተሰኘው የአምፑል ቴክኖሎጂ እየቀየረ መሆኑን አስታውቀዋል። በቅርቡ ከቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ እስከ መስቀል አደባባይ ቤተመንግስት ድረስ የሚዘልቀው የመንገድ መብራት የጸሀይ ብርሃን በሚመስለው በዚህ አይነት የመብራት ቴክኖሎጂ መቀየሩን ጠቁመዋል።

 እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ እነዚህ መብራቶች ከቀድሞው መብራት አንጻር ሲታዩ በውበትም በሀይል ቁጠባቸውም ተመራጭ ናቸው።ረጅም ጊዜ ማገልገልም ይችላሉ።ይህን መሰረት በማድረግም የዋና ዋና መንገዶች መብራት በአዲሱ መብራት እየተቀየረ ነው።

በ2011 በጀት አመት በዚህ ላይ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት በመመደብ የመንገድ ዳር መብራቶችን በአዲስ የመተካት ስራ መሰራቱን አቶ ጥኡማይ ተናግረው፣ከዚህም ገንዘብ ውስጥ ወደ 25 ሚሊዮን ብር በመመደብ የጥገና ሥራ መሰራቱን አስታውቀዋል። በዚህም የተበላሹ እና መብራት የማይሰጡትን የመንገድ መብራቶች መብራት እንዲኖራቸው ለማድረግ በስፋት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ዳይሬክተሩ ለረጅም ጊዜ ሳይበሩ የቆዩት የዊንጌት እንቁላል ፋብሪካ አቡነ ጴጥሮስ አደባባይ መንገድ፣ የቀለበት መንገዶች አብዛኛው የመንገድ መብራት፣ ከኮተቤ ወሰን ግሮሰሪ እስከ ላምበረት ያለው የመንገድ መብራት እንዲገኙ መደረጉን ጠቅሰው፣ ቦሌ አራብሳ፣ ፈረንሳይ ጉራራ አካባቢም በተመሳሳይ ጠፍቶ የነበረው የመንገድ መብራት አገልግሎት እንዲሰጥ መደረጉን አብራርተዋል።እነ የካ አባዶ ደግሞ የመንገድ መብራት እንደገባላቸውም አመልክተዋል።

 የመንገድ መብራቶች በተሽከርካሪ ግጭት እየደረሰባቸው መሆኑን ጠቅሰው፣ አንዱ ሲገጭ አብዛኛው መብራት አገልግሎት የሚያቋርጥበት ሁኔታ እንደሚከሰት ተናግረዋል።በኤሌክትሪክ ምሰሶዎች ግርጌ ላይ በሚገኘው ማዘር ቦርድ ላይ እየተፈጸመ ያለው ስርቆት አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ጠቅሰዋል።

በስርቆቱ ሳቢያ በእቃ ደረጃ ሲታይ የሚደርሰው ጉዳት ትንሽ መሆኑን ጠቅሰው፣ የሚቋረጠው መብራት ጉዳይ ግን አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል።‹‹ይህን ስናይ መብራት እንዲጠፋ የሚፈልግ አካል አለ ማለት ነው። ይህ አይነቱ ስርቆት በጣም እየተስፋፋ ነው።››ሲሉም ገልጸዋል።

‹‹የመንገድ መብራቶች የመንገድ አካል መሆናቸውን ጠቅሰው፣እነሱን መጠበቅ አስፋልቱን መጠበቅ መሆኑንም ገልጸዋል። ወረዳ እና ክፍለ ከተማ እንዲሁም ፖሊስ እና ደንብ ማስከበርን የመሳሰሉ የጸጥታ ሀይሎች ለዚህ ጉዳይ ትኩረት ሰጥተው መሥራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል። ‹‹ህብረተሰቡ የመጠየቅ እንጂ የመጠበቅ ልምድ የለውም።››ያሉት ዳይሬክተሩ ህብረተሰቡ በመንገድ መብራት ላይ ጉዳት የሚያደርሱ አካላት ላይ ክትትል ማድረግ እንደሚኖርበትም አመልክተዋል።

አዉሎ ሚድያ ጥር 12/2012

መልስ አስቀምጥ

Please enter your comment!
እባክዎ ስምዎን እዚህ ያስገቡ