27 የምግብ አይነቶች ከገበያ ታገዱ

0
183

የኢትዮጵያ የምግብ ፣የመድሐኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥር ባለስልጣን አድራሻቸው የማይታወቁና ተጭበርብረው የተሠሩ 27 የምግብ ምርቶቸ አግጃለው አለ፡፡

ባለስልጣኑ ለአዲስ ዘመን በላከው ጋዜጣዊ መግለጫ እንደገለጸው፤ በሁለተኛው ሩብ ዓመት በመላው አገሪቱ ለሕብረተሰቡ በብዛት በሚቀርቡ የምግብ ምርቶች ላይ ቁጥጥር ተደርጓል፡፡ በመሆኑም የአምራች ድርጅቶቻቸው አድራሻ የማይታወቁ፣ ተመሳስለውና ተጭበርብረው የተሠሩ የምግብ ምርቶች ገበያ ላይ እየዋሉ ስለመሆናቸው ማረጋገጥ እንደተቻለ ጠቁሟል፡፡

በተደረገው የገበያ ቅኝት የተሟላ ገላጭ ጽሑፍ የሌላቸው፣ አስገዳጅ ብሔራዊ ደረጃን ያላሟሉ፣ አምራች ድርጅቶቻቸውም ሆነ አድራሻቸው የማይታወቁ፣ መለያ ቁጥር የሌላቸው፣ የመጠቀሚያቸውና የተመረቱበት ጊዜ በትክክል ያልታተመባቸውና የታሸጉ ምግቦች መገኘታቸውን ገልጸዋል፡፡

ከገበያ የታገዱት የምግብ ዓይነቶችም ንጹህ የኑግ ዘይት፣ ኢዛና ዘይት፣ ጣና ዘይት፣ ኦሊያድ ዘይት፣ ስኬት የተጣራ ዘይት፣ በቅሳ የምግብ ዘይት፣ አሚን የምግብ ዘይት፣ቀመር የምግብ ዘይት፣ ሎዛ የምግብ ዘይት፣ ዘቢብ ቃህ የምግብ ዘይት፣ ዘመን የኑግ እና የለውዝ ዘይት፣ ማኢዳ የለውዝ ቂቤ፣ ሮዛ ክሬሚ ለውዝ ቅቤም፣ ዳና ቪንቶ፣ ቪንቶ፣አዋሽ የገበታ ጨው፣ሳራ እና ኑስራ ጨው፣ሴፍ የገበታ ጨው፣ሽናጉ የገበታ ጨው፣ወዛቴ የአይወዲን ጨው፣ቃና የገበታ ጨው፣አስሊ የገበታ ጨው፣ ሲሳይ ንጹህ ማርና ቅቤ፣ ወለላ ማር፣ካርቶንስ ካንዲ ፍሩትስ፣ ሊዛ ሎሊፖፕ እና ክሬም ሎሊፖፕ ተጠቅሰዋል፡፡

የክልል ተቆጣጣሪዎችና በየደረጃው የሚገኙ የቁጥጥር አካላት ምርቶቹን ከገበያ ላይ የመሰብሰብ ሥራውን እንዲሠሩ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ጥሪ ማቅረቡንም አስታውቋል፡፡

ሕብረተሰቡም የትኛውንም የምግብ ምርት ከገበያ ሲገዛ ትክክለኛነቱን ለማረጋገጥ እንዲረዳው የተመረተበትንና የመጠቀሚያ የአገልግሎት ጊዜው ትክክለኛነት፣ የደረጃ ምልክት የለጠፈ፣ ያልተፋቀና ያልተሰረዘ መሆኑን፤ የአምራች ድርጅቱ ስምና ሙሉ አድራሻ፣ የምርት መለያ ቁጥር ያሟላ መሆኑን ማረጋገጥ እንዳለበት ተገልጿል፡፡

ሕብረተሰቡ አጠራጣሪ ጉዳዮች ሲገጥሙትም ለአካባቢው ፖሊስ ወይም ለባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በነፃ ስልክ መስመር 8482 ላይ እንዲያሳውቁ ጠይቋል፡፡

አዉሎ ሚድያ ጥር 8/2012ዓ.ም

መልስ አስቀምጥ

Please enter your comment!
እባክዎ ስምዎን እዚህ ያስገቡ