የህወሓት አንደኛ አስቸኳይ ድርጅታዊ ጉባኤ የአቋም መግለጫ

0
75

በድርጅታችን ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ከታህሳስ 25 እስከ 26/2012 ዓ/ም ለከታታይ ሁለት ቀናት “ፅናትና መመከት ጉባኤ” በሚል መሪ ቃል ያካሄድነው ታሪካዊ አንደኛ አስቸኳይ ድርጅታዊ ጉባኤችን በድል ተጠናቋል። አስቸኳይ ድርጅታዊ ጉባኤችን ቀደም ሲል ሲካሄዱ እንደነበሩ ጉባኤዎች ሁሉ ላለንበት የትግል ምዕራፍ በሚገባ በመገምገም ቀጣይ የትግል አቅጣጫ በማስቀመጥ ፍፁም በሆነ የዓላማ ፅናትና ወኔ ላይ ሆነን ስኬታማ ጉባኤ አካሄደናል።

የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ የምንገኝበት ተጨባጭ ሁኔታ መነሻ በማድረግ የጠራው አስቸኳይ ጉባኤ ተገቢና ጊዜው የጠበቀ እንደሆነ ጉባኤተኛው በሙሉ ድምፅ አፅድቆታል። ባለፉት 27 ዓመታት የአገራችንን የቁልቁለት ጉዞ በመግታት ወደ ለውጥና ዕድገት ያስገባ መስመርና ስርዓት በግላጭ እንዲፈረስ በሚደረግበት፣ በህዝቦች ትግልና መስዋዕትነት የተገነባዉ ህገ መንግስትና ህብረ ብሄራዊ ፌደራል ስርዓት በጠራራ ፀሀይ በሚገዘገዝበት፣ ቀደም ሲል ወደ ነበረው ክፉ የባርነትና የጭቆና ስርዓት የሚመልስ ሁለተናዊ ርብርብ በሚደረግበት፣ በተከታታይ ከሁለት አስር ዓመታት በላይ ሁለተናዊ አንፀባራቂ ልማትን በማስመዝገብ፣ ለአፍሪካም ሳይቀር የሰላም ዋስትና በመሆን የአገራችን ምስል በበጎ የቀየረ ኢህአዴግ፣ ከስርዓትና አሰራር ውጭ እንዲፈርስ በማድረግ አዲስ ፓርቲ መስርተዋል።

እኛ አጥብቀን የያዝነውን ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መስመራችንን ለማስቀጠልና በየጊዜው የሚገጥሙንን ፈተናዎች እየፈታንና እየታደስን ያላሰለሰ ትግል በምናካሂድበት ወቅት፤ ሌሎች ግን የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመር አጥበቀው ይዞ በፅናት ሲጓዝ የነበረውን ኢህአዴግ በማፍረስ፣ የዚች አገር ተጨባጭ ችግርና ሁኔታ በመካድ አዲስና የተገዛ ጥገኛ ፓርቲ በህገ ወጥ መንገድ እንዲመሰረት አድርገዋል። በጋራ ሆነን ኢህአዴግን በመመስረትና በማጠናከር ሲሰሩ የነበሩ ድርጅቶች መስመሩን በመካድ ወደ ሌላ ጥገኛ ጎራ ተሸጋግረዋል። ይህ ክህደት የተፈፀመው በመስመሩና በዓላማው ላይ ብቻ አይደለም። እነሱን አምኖ፣ የኢህአዴግ ዓላማ ተቀብሎ ስልጣን እንዲይዙ በፈቀደላቸው ህዝብም ላይ ጭምር ነው ታሪክ የማይረሳው ክህደት የፈፀሙት።

ለዚህም ነው፤ ህወሓት በመርህና በህጋዊ አሰራር ተመስርቶ የፀና አቋም በመያዝ፣ ይህንን የክህደት ተግባር በፅናት ሲታገል የቆየው። ድርጅታችን ህወሓት እስካሁን ሲያካሂደው የነበረዉ ትግል፣ ከኢህአዴግ መፈረስና አዲስ ጥገኛ ፓርቲ ከመመስረት ተያይዞ የህወሓት ስራ አስፈፃሚና ማእከላይ ኮሚቴው የወሰዱት አቋም ተገቢና መርህን የጠበቀ ነው። አገራችን ለማፍረስ፣ ህገ መንግስቱና ህብረ ብሄራዊ ፌደራል ስርዓቱን ለመናድ ተባባሪ ላለመሆን ስንል ኢህአዴግ በማፍረስም ይሁን አዲስ ኢ-ህጋዊ ፓርቲ በመመስረት ተግባር ላይ ልንሰማራ አንችልም።ልዩነታችን መስመር ነው። ልዩነታችን ስርዓቱ በማስቀጠልና ስርዓቱን በማፍረስ ጥያቄ ላይ የተመሰረተ ነው። ልዩነታችን የአገራችን ሁሉም ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በእኩልነት የሚኖሩባት ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት በሚጥርና እና ይህንን ተጨባጭ ሀቅ በመካድ አሃዳዊ ስርዓትን ለመትከል በሚካሄድ ትግል መካከል ነው።

ህወሓት ይህንን እምነትና አቋም በመያዙ ምክንያት እየተካሄደበት የቆየና አሁንም እየቀጠለ የሚገኝ የስም ማጥፋት፣ የማጠልሸትና ሴራ ቀላል አይደለም። አላሳልፍ ብለው ከለከሉን የሚሏቸውን ህወሓትና የትግራይ ህዝብን ለማንበርከክና አንገታቸውን ለማስደፋት ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም፤ ለወደፊትም ይህንን ከማድረግ ወደ ኋላ አይሉም። ይህንን ሁሉ ሴራና ተፅዕኖ ለመመከት በፍፁም አንምበረከክም! ዳግማዊ ባርነት መቸው አንቀበልም ብለን ልንሰማራ በተገደድንበት ጊዜ ላይ እንገኛለን። በፍፁም አንምበረከክም እያልን ያለነው ልንል ስለፈለግን ብቻ እየተጠቀምንበት ያለው አባባል አይደለም። ወይም ከዚህ ይህ ይሻላል ብለን እያማረጥን ስለሆነም አይደለም። ከዚህ ቀደም የከፈልነው መስዋእትነትና የትግል ፅናት ተማምነን ኣይደለም እያልን ያለነው። መከራ ማሳለፍ፣ በመከራ ተፈትኖ የሚያልፍ ህዝብና ድርጅት ስላለን ብቻም አይደለም። በዚህ ጊዜ ያጋጠመን ፈተና በፅናት ታግለን ከማለፍ፣ በፍፁም ወዳለፈው ባርነት አንመለስም ብለን ከመታገል ውጪ ሌላ አማራጭ ስሌለን ጭምር ነው። ያለፈው መከራና ውጣ ውረድ አልፈን፤ ማለቂያ የሌለው መስዋእት ከፍለን፤ እንደ ጎርፍ የፈሰሰው ደም ሳይደርቅ፤ ብርቅዬ የህዝብ ልጆች በለጋ ዕድሜአቸው ህይወታቸው ገብረው፤ አካላቸውን ከስክሰው የተገነባ ስርዓትና መስመር ወደ ኋላ ተቀልብሶ ዳግም ወደ ባርነት ፈፅሞ መግባት ስለሌለብንም ነው።

ይህ ፈተና ከሩቅ የምናየው አይደለም። ከፊታችን ተገትሮ ያለ የሚታይ የነገ ሳይሆን የዛሬ ፈተና ነው። ይህ ፈተና እንዳለፈው ፀንተን ታግለን ከመከትነው የሚነቀንቀን፣ እስከወድያኛው ሊበታትነን የሚፈልግና የሚችል ሃይል አይኖርም። እዚህ ላይ ስህተት የፈፀምን እንደሆነ ግን ለቀጣይ በርካታ ዓመታት ወደ ከፋ መከራ የማንገባበት ምንም ዓይነት ምክንያት አይኖርም። ይሄን ያህል ህልውናችንን በሚወስን የትግል ምዕራፍ ላይ እንገኛለን።

የማንሻገረው የማናልፈው ፈተናና ችግር ሊኖር አይችልም። እየታደሰና እየጎለበተ የሚሄድ የጠራ መስመር ይዘን፤ በዚህ ጥራት ያለው መስመር ጥላ ስር ተሰልፎ ተአምር የሚሰራ ፅኑ ታጋይ ህዝብ ይዘን እናልፈዋለን። ዛሬ ጨለምለም ያለ ቢመስልም በትግላችንና በፅናታችን ነገ ጨርሶ ይነጋል። ትላንት እንኳን ርሃብ፣ መከራና ግፍ ሳይበግረው፣ የሰው ልጅ ሊቋቋመው ይችላል ተብሎ ከሚገመተው በላይ ተቋቁሞ ወደ ድል የደረሰ ህዝብ ዛሬ አንገቱን የሚደፋበት ምክንያት በፍፁም ሊኖር አይችልም።

የትግራይ ህዝብ ቅርስና አሻራ ትዕግስት፣ ቻይነት፣ ብልሃት፣ ትግል፣ ፅናትና ድል ድራጊነት ነው፡፡ አሁንም ቢሆን ፍትሃዊ ትግል እስካካሄድንና የጠራ መስመራችንን እስከያዝን ድረስ ያለጥርጥር እናሸንፋለን፡፡ ችግሮችን የመፍታትና የመሻገር፣ በችግሮች ላይ አዲስ ጥንካሬ ይዞ የመውጣት ፅናትና ተሞክሮ ያለው ድርጅታችንና ህዝባችን ይዘን የማንሻገረው ወንዝ የለም፡፡ ፍፁም አንበረከክም ብለን ለዳግማይ ድልና ለዳግማይ ታሪክ ተነስ ተሰማራ ብለን የምንሰማራበት ጉባኤ ነው፤ “የፅናትና መመከት ጉባኤ”።

በዚሁ የመጀመሪያ አስቸኳይ ጉባኤያችን በባለፈው 13ኛው መደበኛ ጉባኤ በድምፅ ከተመረጡ 1174 ተወካዮች ውስጥ 1116 ማለትም 95 በመቶ የተገኘን ሲሆን ጉባኤውን ለማዘጋጀት የተሰየመው አዘጋጅ ኮሚቴ ባቀረበው ሪፖርትና አጀንዳ በሙሉ ድምፅ በማፅደቅ ተጀምሯል፡፡ በዚህም መሰረት ይህ አስቸኳይ ጉባኤ የተመለከታቸው የሚከተሉትን ሶስት ዓበይት አጀንዳዎችም፡-

አሁን ያለው የሀገራችንንና የክልላችንን ፖለቲካዊ ሁኔታ ከዚህ በተዛመደ የኢህአዴግ መፍረስና የአዲሱ ህገ ወጥ ብልፅግና ፓርቲ መፈጠርን በሚመለከት በማእከላዊ ኮሚቴ የቀረበ ሪፖርት፤

ከኢህአዴግ ጋር የነበረን ግንኙነት የምርጫ አዋጅና ምዝገባ ፓለቲካዊ ፓርቲዎችና የምርጫ ስነ ምግባር መሰረት ያደረገ የመተዳሪያ ደንብ ማሻሻያ፤

ከኢህአዴግ ጋር የነበረን ትስስርና እያደገ ከመጣው አዲስ ሁኔታ መሰረት ያደረገ የፕሮግራም ማሻሻያ ናቸው፡፡

በነዚህ አጀንዳዎች በጥልቀትና በዝርዝር ተወያይተን በሙሉ ድምፅ ስምምነት ላይ ደርሰናል። በመሆኑም ካለንበት ተጨባጭ ሁኔታና ወደፊት ከሚኖረን ትግል መነሻ በማድረግ አንደኛ አስቸኳይ ጉባኤያችን የሚከተሉትን ባለ 8 ውሳኔዎችን ወስኗል።

ላለፉት 30 ዓመታት በትጥቅ ትግል ይሁን በልማት፣ በሰላምና በዲሞክራሲ ትግላችን የሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ በመረዳት መፍትሄ ያመጣው መስመርና አደረጃጀት በብቃት መልሰን በጋራ ኢህአዴግን መስርተን ወዳጅም ጠላትም የሚያውቀው ተአምራዊ ድሎችን እያስመዘገብን ቆይተናል፡፡ ይህ የሀገር ድልና ደህንነት ያስጠበቀ መስመርና አደረጃጅት ህልውናው ተረጋግጦ አገራችንን ወደላቀ ከፍታ እንድትወጣ የድርጅታችን ምኞትና ፍላጎት የነበረ ቢሆንም ተፈጥሮ በቆየውና አሁንም ባለው የኢህአዴግ ጥገኛና የመበስበስ ባህሪ ኢህአዴግ ሃዲዱን ስቶ ወደ አዲስና በይዘቱ ልዩ የሆነ ጥገኛ ፓርቲ ተሸጋግሮ ይገኛል፡፡ በመሆኑም ያ በጋራ የፈጠርነው ኢህአዴግ ከግንባሩ ስርዓትና አሰራር ውጭ በሶስቱም ድርጅቶች ክህደት እንዲፈርስ ተደርጓል። አስቸኳይ ጉባኤያችንም ይህንን ህገ-ወጥና ፀረ- ዴሞክራሲ ተግባር እየኮነነ ህወሓት ግን ይዞት የነበረውን መስመር፣ እምነቱንና አደረጃጀቱን ይዞ በፅናት ይቀጥላል፡፡ ከዚህ ባለፈም ከተፈጠረው አዲስ ህገ- ወጥ ብልፅግና ፓርቲም ጋር በያዝነው መስመርና አስተሳሰብ አብረን መሄድ ፈፅሞ አንችልም፡፡ በዚሁ ምክንያትም ማእከላዊ ኮሚቴ ይሁን ስራ አስፈፃሚ የወሰደው አቋም ትክክለኛና ተገቢ ነበር፡፡ በመሆኑም ህወሓት ሀገርን የማፍረስ አካል ላለመሆን ከተባለው ህገ-ወጥ ጥገኛ ፓርቲ ጋር እንደማይዋሃድና እንደማይቀላቀል አስቸኳይ ጉባኤያችን ወስኗል፡፡

ለመስመራችንና ለህዝባችን ደህንነት ብለን እስካሁን ያካሄድነው ትግል የተሳካ ነበር፡፡ ለወዲፊቱም ቢሆን በሰላማዊ፣ በህጋዊና በዲሞክራሲያዊ አገባብ ለህልውናችንና ለደህንነታችን ስንል ሁለንተናዊ ትግል ልናደርግ የትግራይ ራስን የማስተዳደር ቀጣይነት ለማጎልበት መላ ህዝባችንና ኣባላሎቻችን ለዚሁ ልዩ የትግል ምዕራፍ ከነሱ የሚጠበቀውን ሁሉ ለመፈፀም ድርጅታችን ከፊት ሆኖ መሪ ሚናውን እንዲጫወት አስቸኳይ ጉባኤያችን ወስኗል፡፡

ለህዝባችን ህልውናና ደህንነት ሲባል በሚደረገው ሁለገብ የመመከት ተግባር በትግራይ ውስጥ ከሚገኙና የትግራይ ህዝብ ደህንነትን ለድርድር ከማያቀርቡ ከፖለቲካዊ ድርጅቶች፣ ከስቪክ ማህበራት፣ ከህዝብ አደረጃጀቶች፣ ከግለሰቦች ወዘተ ጋር አብሮ ለመስራት የተለየ የትግልና የአደረጃጀት አገባቦችን በመጠቀም ለመደገፍና ለመተጋገዝ ከፍተኛ ጥረት እንዲደረግ አስቸኳይ ጉባኤያችን ወስኗል፡፡

በያዝነው መስመር፣ አስተሳሰብና እምነት ተለያይተናል ማለት በህዝባችንና በሀገራችን ጉዳይ ላይ ግንኙነት አይኖረንም ማለት አይደለም፡፡ ልዩነታችንን አክብረን ሓሳቦቻችንን በሰላማዊ፣ በህጋዊና በዴሞክራያሲዊ መንገድ መራመድ እንችላለን፡፡ መሆን ያለበት ስልጡን አካሄድም ይኸው ነው፡፡ በመሆኑም ህወሓት በህገ መንግስታዊና በህብረ ብሄራዊ ፌዴራሊዝም ስርዓት ስር ሆኖ በፅናት ይታገላል፡፡ ህወሓት የሚመራው ክልላዊ መንግስት ከፌዴራል መንግስት ጋር ያለው ግንኙነት ለሁለቱም መንግስታት የተሰጣቸው ህገ መንግስታዊ ሀላፊነት መሰረት በማድረግ እንዲቀጥልና እንዲሰራ ከዚህ ውጭ ለሚመጣው ማንኛውም ዓይነት ጫና፣ ተግባርና እንቅስቃሴ እንዲኖር ፈፅሞ እንደማንፈቅድ፤ ዛሬም እንደወትሮው ሁሉ በፅናት ለመታገልና ለመመከት አስቸኳይ ጉባኤያችን ወስኗል፡፡

ለብሄራዊ ጥቅማችንና ለጋራ ሀገራዊ ጥቅማችን ብለን የሀገራችንን ህገ መንግስታዊና ፈዴራላዊ ስርዓት ህልውናና ዋስትና ለማረጋገጥ በሚደረገው ትግል እኛን ከመሰሉ ህገ መንግስታዊና ህብረ ብሄራዊ ፌዴራሊስት ኃይሎች በሀገራችን ምርጫ ህግ መሰረት ሁሉም የአደረጃጀት ዓይነቶች ተጠቅመን ማለትም ፎረም፣ ሕብረት፣ ግንባር፣ ውህደት እስከ መፍጠር የሚሄድ ትግልና መደጋገፍን ለማድረግ ለዚህ ታክቲካል መድረክ የሚሆን ሰፊ ግንባር በመፍጠርና በልማታዊና በዴሞክራያዊ መስመር ላይ እምነት ካላቸው ኃይሎች ደግሞ ስትራቴጂክ ግንባር እንዲኖረን የሚያስችል ህገ ደንባችን በሚያዘው መሰረት እንዲፈፀም አስቸኳይ ጉባኤያችን ወስኗል፡፡

ኢህአዴግ የፈረሰበት አግባብ ህገ-ወጥና ፀረ- ዲሞክራሲያዊ አካሄድ ነው፡፡ ሂደቱም ከምርጫ አዋጅ፣ ከፖለቲካዊ ድርጅቶች ምዝገባና ከሀገራችን ምርጫ ስነ-ምግባር፣ ከግንባሩ መተዳደሪያ ደንብ ውጭ በፀረ- ዲሞክራሲ መንገድ እንዲፈርስ ተደርጓል፡፡ ይህንን ተከትሎ ከኢህአዴግ ጋር የነበረንን ግንኙነት ኢህአዴግን ለማፍረስ የተኬደበት ህገ-ወጥ አግባብና የነበረንን የጋራ ሃብትና ንብረት መሰረት ያደረገ መብታችንንና ጥቅማችንን ለማረጋገጥ ማንኛውም ዓይነት ሕጋዊ መንገድ ሁሉ እንጠቀማለን፡፡ በአስቸኳይ ጉባኤያችን የተወሰኑ ውሳኔዎች የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ በሰላማዊ፣ በፖለቲካዊና በህጋዊ አግባቦች እንዲፈፀም አስቸኳይ ጉባኤያችን ወስኗል፡፡

የትግራይ ህዝብ ለህልውናውና ለደህንነቱ ብሎ ባካሄደው ሁለገብ የመመከት እንቅስቃሴ፣ ዕንቅፋት የሆኑትን ውስጣዊ ድክመቶቻችን ማለትም ጎጠኝነት፣ በተለያዩ መልክ የሚታዩ ኋላቀርነት፣ ሃይማኖትን ምክንያት ያደረገ ፅንፈኛ እንቅስቃሴ የትግራይ ህዝብን ፖለቲካዊ አንድነት የሚያደፈርስ ከውጭና ከውስጥ የሚመጣ አስተሳሰብና ተግባር በፅናት መታገል ከመቸውም ጊዜ በላይ ዛሬ አስፈላጊ ሆኗል። የውስጣችንን ድክመቶች ተጠቅመው የትግራይ ህዝብና የህወሓት አንድነትን በማደፍረስ የህዝባችንና የድርጅታችንን ህልውናና ደህንነት ወደ ገበያ በማውረድ በፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ስም ወደ ንግድና ሸቀጥ የተሰማሩትን እንክርዳዶችና ባንዳዎች እያደረጉት ያሉትን ፀረ- ህዝብ እንቅስቃሴ ፈፅሞ ዕድል በማይሰጥ መልኩ ለመመከት የላቀ ትግል እንዲደረግ፤ መላ ህዝባችንና የድርጅታችን አባሎች ዛሬም እንደወትሮው በእምነታችን ፀንተን ነገ ለማይቀረው ድላችን አንድነታችንን አጠናክረን በመስመራችን ዙሪያ ተሰልፈን ፖለቲካዊ አንድነታችንን ወደ ላቀ ከፍታ ለማሸጋገር ሁለንተናዊ ትግል እንዲደረግ አስቸኳይ ጉባኤያችን ወስኗል፡፡

አስቸኳይ ጉባኤያችን የወሰናቸው ውሳኔዎች በሙሉ ማእከላዊ ኮሚቴው ኃላፊነት ወስዶ እንዲዘረዝርና እንዲፈፅም አስቸኳይ ጉባኤያችን ወስኗል ፡፡

የተከበርከው በአገር ውስጥና በውጭ የምትኖረው የትግራይ ህዝብ፡- አርሶአደር፣ ወጣት፣ ሴቶች፣ በውጭ አገር የምትኖሩ፣ የከተማ ኗሪ፣ ምሁር፣ ነጋዴዎችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በሙሉ፡-

በከፈላችሁት መራራና ክቡር መስዋእትነት በሀገራችን ላይ ተጭኖ የቆየውን አሃዳዊና ጨፍላቂ ስርዓት ደምስሰህ በእኩልነታዊ አንድነት የተመሰረተ ህብረ ብሄራዊ አገርና ስርዓት በመገንባት ረገድ የላቀ አስተዋፅኦ አበርክተሃል፡፡ ወደር የሌሽ መስዋእትነት ከፊያለው ብለህ ትርፍ ሳትጠብቅ በጥረትህና በላብህ አካባቢህንና ሃገርህን በማልማት እኩል የመጠቀም መብትህን ለማረጋገጥ እና የጦርነት ብቻ ሳይሆን የልማት አርበኝነትህንም በተግባር አረጋግጠሃል።

ይሁን እንጂ ባካሄድከው ትግል ያሸነፍካቸው ከዚህም ከዚያም ተሰባስበው በትምክህት ፊታውራሪነት በከባድ መስዋእትነት የተገነባውን ሕብረ ብሄራዊ ፌዴራልዝም ስርዓት ለመናድ በሚያካሂዱት ትንቅንቅ፣ ህወሓትና የትግራይ ህዝብ እንደ ዋነኛ ጠላታቸው በማስቀመጥ ከሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች ለመነጠል እጅግ በጣም ሰፊና ተከታታይ የማጠልሸት ዘመቻ እያካሄዱ ቆይተዋል፣ አሁንም እያካሄዱ ነው። እጅግ በርካታ የትግራይ ተወላጆች ከነበሩበት አካባቢዎች ለአዓመታት ጥሮና ግሮ ያፈራውን ንብረቱ እየነጠቁ እንዲፈናቀሉ አድርገዋል። ገድለዋልም። ስርአት በመገንባት እና የሀገር ዋስትና በማስጠበቅ ሂደት ላይ እጅግ በጣም የላቀ አስተዋፅኦ የነበራቸው የትግራይ ተወላጆች አለአግባብ በእስር ቤት እንዲማቅቁ አድርገዋል፣ የትግራይ ህዝብ ግን ሁሉንም ችለህ ተመሳሳይ እኩይ የአፀፋ ምላሽ ልስጥ አላልክም ፣ ለዚሁም ተግባርህ የላቀ ክብር ይገባሃል። በዚህ በነደፉት ቀጥተኛ ጥቃት ድል ማስመዝገብ ስላልቻሉ፣በሃይማኖትና በጎጠኝነት አንድነትህን ለማደፍረስ ብሎም ለማምበርከክ ሰፊ ዘመቻ እያካሄዱ ነው።

አሁንም ቢሆን የጠበቁት ሳይሆን ቀርቶ፣ አንድነትህን ይበልጥ አጠናክረህ የማትበገር ህዝብ መሆንክን በተግባር አሳይታሃቸዋል። ነባራዊው የሀገሪቱ ሁኔታዎችን በተወካዮችህ በኮንፈረንስ አማካኝነት የሰጠኸን ምክርና ሀሳቦች፣ በተካወካዮችህ አማካኝነት ያሳለፈከውን ውሳኔ መሰረት በማድረግ፣ አሁንም ፍንክች አንልም በማለት በቁጭት ለአንደኛው አስቸኳይ ጉባኤያችን ውሳኔዎች የላቀ ድጋፍ በመስጠት፣ መስመርህን አጥብቀህ በመያዝ፣ አንድነትህን በማጠናከር፣ ለማይቀረው ድል ተነስ፣ ዛሬም እንደወትሮው ሁኔታዎችን በንቃትና በተጠንቀቅ ልትከታተላቸውና ለማይቀረው ድል እንድትገሰግስ ጉባኤያችን ጥሪውን ያቀርባል።

2.የተከበራችሁ የህወሓት አመራሮችና አባላት !

በድርጅታችሁ መተዳደርያ ደንብ መሰረት ከአባልነት እስከ የህይወት መስዋእትነት ግዴታችሁ ለመወጣት በፅኑ አምናችሁ፣ ድርጅታችሁ በትምክህተኞችና ጥገኞች ሴራና ተፅእኖዎች እንዳይበተን፣ የትግራይ ህዝብም ያለመሪ እንዳይቀር እንደብረት ጠንክራችሁ፣ “በሬው ወዴትም ይጓዝ እርፍን አጥብቀህ ያዝ” በሚል በከባድ የህዝብ ልጆች መስዋእትነት የተመሰረተውን ህገ መንግስትና ፌዴራላዊ ስርዓት ለማዳን እያደረጋችሁ ያለውን ትግልና እያሳያችሁት ያለው ፅናት፣ የትግራይ ህዝብ ለማጎሳቆል ተይዞ የነበረውን አጀንዳ ፍጥነቱ እንዲቀንስ፣ ህዝባችሁ ሁኔታዎችን በአግባቡ እንዲረዳ አድርጋችዋል። አሁንም የሀገሪቱ ሁኔታ ከከፋ ወደ ባሰ እየተሸጋገረ ባለበት ወቅት፣ ይበልጥ ከብረት የጠነከረውን ጽናታችሁን ተላብሳችሁ የአንደኛው አስቸኳይ ጉባኤያችን ውሳኔዎች ተግባራዊ ለማድረግ እና በልማት ሰራዊት ግንባታና የመመከት አቅጣጫ የመሪነት ድርሻችሁን እንድትወጡ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

3. የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች እንዲሁም የሕብረ ብሄራዊ ፌዴራልስ ሃይሎች!

ባለፉት 27 አመታት በአንድ ልብ ያደረጋችሁት ትግል፣ በእኩልነት ላይ የተመሰረተ አንድነት እንዲሁም ሕብረ ብሄራዊት ሀገርና ስርዓት መስርታችሁ፣ሁሉም በየደረጃው ፍትሃዊ ተጠቃሚ ያደረገ እና መላ ዓለም የመሰከረለትን ልማት ማረጋገጥ ችላችኋል። ይህ ያልተዋጠላቸው የትምክህትና ጥገኛ ሃይሎች ስርዓቱን በማፍረስ ወደኋላ ሊመሉሱት፣ የተመዘገቡት ድሎችና ተስፋዎች እንዲጠፉ ከፍተኛ ርብርብ እያደረጉ ነው። ሰላማችሁ ደፍርሶ፣ የዜጎች መፈናቀል በዝቶ፣ ሀገር በመበታተን ጫፍ እንድትደርስ እያደረጉ ነው። በሀገራችን ያንዣበበውን አደጋ ለመመከት እንዳትችሉ እየተደረጉ ያሉትን ተፅእኖዎችና ማስፈራሪዎች በመሻገር ወደ አፄዎቹ ስርዓት መመለስ እንደማትፈልጉ በአደባባዮች ሳይቀር እየወጣችሁ ተቃውሟችሁን እያሰማችሁ ነው። አሁንም የጀመራችሁትን ትግል አጠናክራችሁ ወደ ላቀ ደረጃ እንድታሸጋግሩ ጥሪያችንን እያቀረብን፣ የትግራይ ህዝብና ህወሓት ከጎናችሁ መሆናችንን ጉባኤያችን ያረጋግጥላችኋል።

4. የተከበርክ ወንድም የኤርትራ ህዝብ!

እንደሚታወቀው የትግራይና የኤርትራ ህዝብ በጋብቻ፣በቋንቋ፣ በባህል ተመሳሳይና ወንድም ህዝቦች ናቸው። የጋራ ጠላት የነበረውን ፋሽሽት ደርግ ስርዓት ለመደምሰስም በጋራ ደምተናል፣ መስዋእት ከፍለናል፣ በአንድ ጉድጓድም ጀግኖች የህዝብ ታጋዮች ቀብረናል።

በእንዲህ ዓይነት የመተጋገዝ መንፈስ የትግራይ ህዝብና ህወሓት ለኤርትራ ህዝብ ነፃነት እና ራስን በራስ የመወሰን ሙሉ መብት ድጋፍ ሰጥቷል፣ መስዋእትነትም ከፍሏል። ይሁን እንጂ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በሁለቱ ወንድማማቾች ህዝቦች አብረው በሰላምና ልማት ከመጠቀምና ከመበልፀግ ይልቅ አላስፈላጊ ጦርነት ውስጥ ገብተን ትልቅ ኪሳራ ከፍለናል።

ይህ ያጋጠመው ጠባሳ ለመሻርና ለመፈወስ ወደ ነበረበት ሰላም ለመመለስ የትግራይ ህዝብና ህወሓት ያላሰለሰ ጥረት ሲያደርጉ ቆይቷል። ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል በሁለቱ ሀገራት መሪዎች የተጀመረው ግንኙነት ተስፋ ሰጪ የነበረ ቢሆንም፣ በሂደት ግን ግልፅ ባልሆነ መንገድ ያ የተጀመረው ግንኙነት ሊቋረጥ ችሏል።

ይህ የተጀመረው ተስፈ ሰጪ ወድማማችነትና ዝምድና በትብብር ማእቀፍና ሁላችንን የሚጠቅም እንዲሆን፣ ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን የትግራይ ህዝብና ህወሓት ከነሱ የሚጠበቀውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ደግመን እናረጋግጣለን። የኤርትራ ህዝብም በበኩሉ ለዚህ ሰላም ዘላቂና አስተማማኝ እንዲሆን እና እንዲጠናከር የራሱ በጎ ድርሻ እንዲጫወት ጥሪያችንን እናቀርባለን።

5.የሀገራችንና የቀጠናችንን ጉዳይ ያገባናል ለሚሉ የውጭ መንግስታትና ሃይሎች!

አንዳንድ የውጭ ሃይሎች በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በሀገራችና በህዝባችን ላይ እየፈፀሙት ያሉት አሉታዊ ሚና የሀገራችንንና የአካባቢያችንን ሰላምና ጥቅም የሚጎዳ መሆኑን ተረድተው፣ ከውስጣዊ ጉዳዮቻችን እጃቸው እንዲያወጡ፣ ይህ በማይሆንበት ወቅት ደግሞ ለሚፈጠረው ችግር ሃላፊነት እንደሚወስዱ መታወቅ አለበት እንላለን።

የአፍሪካ መንግስታትና የአፍሪካ ሕብረት ይህንን የውጭ ጣልቃ ገብነት ተረድተው አወንታዊ አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

መስመራችን አጥብቀን ይዘን እንመክት!!

አሁንም ሃይላችን ህዝብ ነው! እምነታችን መስመር ነው!

ዘልኣለማዊ ክብርና ሞገስ ለትግሉ ሰማእታት!

የፅናትና መመከት ጉባኤ

ታሕሳስ 26/ 2012 ዓ/ም

መ ቐ ለ

መልስ አስቀምጥ

Please enter your comment!
እባክዎ ስምዎን እዚህ ያስገቡ