በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር 878 የዳስ ትምሀርት ቤቶች አሉ፡፡

0
65

በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ከሚገኙት 878 ትምህርተ ቤቶች ውስጥ ከ133 በላይ የዳስ ጥላ መማሪያ ክፍሎችን ወደ ዘመናዊ ግንባታ ለመቀየር እየተሰራ መሆኑን የብሔረሰብ አስተዳደሩ ትምህርት መምሪያ አስታውቋል፡፡

የዳስ መማሪያ ክፍሎችን ወደቋሚ መማሪያ ህንጻዎች ለመቀየር እየተሰራ ያለው ከሰቆጣ ቃልኪዳን በተገኘ የበጀት ድጋፍ መሆኑ ታውቋል።

ባለፈው ዓመት የክልሉ ትምህርት ቢሮ፣ የዋግ ልማት ማህበርና አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ ባደረጉት የገንዘብ ድጋፍ 336 የዳስ መማሪያ ክፍሎችን ወደዘመናዊ መማሪያ ክፍል ለመቀየር መቻሉን አስታውሰዋል።

በመምሪያው የሰቆጣ ቃል ኪዳን ተጠሪ አቶ ፋንታው ስዩም እንዳሉት በብሔረሰብ አስተዳደሩ በአጠቃላይ ከ878 በላይ የዳስ ጥላ የመማሪያ ክፍሎች አሉ።

“የተገኘውን ልምድ በመቀመር በዚህ ዓመት የሰቆጣ ቃል ኪዳን ፕሮጀክት በመደበው ከ42 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጭ 133 የዳስ ጥላ የመማሪያ ክፍሎችን ወደ ዘመናዊ መማሪያ ክፍል ለመቀየር እየተሰራ ይገኛል” ብለዋል።
የመማሪያ ክፍሎች በብሔረሰብ አስተዳደሩ በሚገኙ ስምንት ወረዳዎች ውስጥ የሚገነቡ ሲሆን የግንባታ ሥራውም ከመጪው ጥር 2012 ዓ.ም ጀምሮ እንደሚጀመር ተናግረዋል።

ህብረተሰቡን በማስተባበር ግንባታውን በአራት ወራት ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ለማከናወን እንደታቀደም ነው አቶ ፋንታው የገለጹት፡፡
እንደእሳቸው ገለጻ የዳስ ጥላ መማሪያ ክፍሎች ወደ ዘመናዊ የመማሪያ ክፍሎች እንዲቀየሩ መደረጉ ህጻናት ይገጥማቸው የነበረውን የትራኮማ እና ሌሎች ተያያዥ ህመሞች ይታደጋቸዋል፡፡
በመማሪያ ክፍሎቹ የግንባታ ሂደትም ከ165 በላይ ምሩቃን ወጣቶች
የሥራ እድል ይፈጠርላቸዋል፡፡

ኢዜአ እንደዘገበው የሰቆጣቃል ኪዳን ከመማሪያ ክፍሎች ግንባታ በተጨማሪም በ75 የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ የምገባ መርሃ ግብር እንደሚጀምር ታውቋል።
ይህም ስር የሰደደ ድህነት እና በስርዓተ ምግብ እጥረት በህጻናት ላይ ይደርስ የነበረውን የመቀንጨር ችግር ለመቅረፍ ያለመ መሆኑ ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በሃገሪቱ የሚስተዋለውን የህጻናት የመቀንጨር ችግርን ለመፍታት መንግስት በሰቆጣ ቃል ኪዳን ስምምነት የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመንደፍ ዕቅድ አውጥቶ እየሰራ ይገኛል።

አውሎ ሚድያ ታህሳስ 27/2012 ዓ/ም

መልስ አስቀምጥ

Please enter your comment!
እባክዎ ስምዎን እዚህ ያስገቡ